የቢታኒያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ

የቢታኒያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ

የቢታኒያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ

ቢታኒያ ቤተ ክርስቲያን ከመፈጠሯ ከረጅም ጊዜ በፊት፣ "የምዕራብ አዲስ አበባ የሰንበት ት/ቤት ምሩቃን ኅብረት" የተባለ የወጣቶች ቡድን ነበር። አባላቱ በቅዱስ ቄርቆስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የሚሰበሰቡ የኦርቶዶክስ ወጣቶች . . .

Bethany

የቢታኒያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ

የሰንበት ት/ቤት ምሩቃን ኅብረት

ቢታኒያ ቤተ ክርስቲያን ከመፈጠሯ ከረጅም ጊዜ በፊት፣ "የምዕራብ አዲስ አበባ የሰንበት ት/ቤት ምሩቃን ኅብረት" የተባለ የወጣቶች ቡድን ነበር። አባላቱ በቅዱስ ቄርቆስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የሚሰበሰቡ የኦርቶዶክስ ወጣቶች ነበሩ።

በኅብረቱ ውስጥ በተለያዩ ቅዱሳን ስም የተሰየሙ ኢ-መደበኛ የቤት ማኅበራት ተቋቁመው ነበር: የአቡነ ረጋዊ ማኅበር፣ የቅዱስ ገብርኤል ማኅበር፣ የቅድስት ማርያም ማኅበር። እያንዳንዱ ማኅበር በተለያየ ቀን፣ በተለያየ ቤት ስለሚሰበሰብ፣ ወጣቶቹ ከቤት ቤት ይዞራሉ የመድኃኔዓለም ሲሆን በአንድ ቤት፣ የማርያም ሲሆን በሌላ ቤት፣ የአቡነ ረጋዊ ሲሆን ደግሞ በሌላ ቤት ይገናኛሉ። በዚህ ምክንያት፣ ኅብረቱ ጥልቅ የሆነ የእርስ በርስ ትውውቅና ወዳጅነት መሥርቶ ነበር።

በዚያው ወቅት የቅዱስ ጳውሎስ ኮሌጅ የመጽሐፍ ቅዱስ ት/ቤት (Bible School) ተማሪዎች በዚህ መንፈሳዊ ማኅበረሰብ ውስጥ ጉልህ ሚና ይጫወቱ ነበር። ከወንጌላውያን አገልጋዮች ጋርም ጥብቅ ግንኙነት ስለነበራቸው፣ እንደ ዘማሪ መንግሥቱ እና አባይነህ ሆዴ ያሉ ታዋቂ ዘማርያን በምሽት ፕሮግራሞች ላይ እየጋበዟቸው ያስተናግዷቸው ነበር። እነዚህ አገልጋዮች በቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን፣ በማኅበራቱ ጉባኤዎች ላይም እየመጡ ያገለግሉ ነበር።

ከዚህ የጋራ ሕይወት ጀርባ፣ መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብና ክርስቶስን በግል የመከተል ቁርጠኝነት በወጣቶቹ ልብ እያደገ መጣ።

 

ለጸሎት የመገናኘት ናፍቆት

ምንም እንኳን የቤት ማኅበራት ሕይወት ሕያው ቢሆንም፣ አብዛኛው መሰብሰቢያ መደበኛ ያልሆነ ብዙ ጊዜ የልጅነት ጨዋታ፣ ሣቅ፣ የተራ ወሬ የተቀላቀለበት ነበር። ይህ ቦታ ቢኖራቸውም፣ የተወሰኑ ወጣቶች በሁለመናቸው ለጸሎት የተወሰነ ራሳቸው ቤት እንዲኖራቸው ይመኙ ጀመር።

ስለዚህ በኢ-መደበኛ መንገድ ራሳቸውን አደራጅተው ጀመሩ። ይኸውም የመጀመሪያው የጸሎት ቤት ተብሎ የሚታወቀው ነው። በሻይ ቤትና በውጪ ቦታዎች ከመገናኘት ይልቅ፣ የጸሎትና የቃል ኅብረት የሚደረግባት የራሳቸው ቤት ሆነችላቸው።

 

የስሟ መነሻ፡ "ቢታኒያ" እንዴት ተባለች?

ለረጅም ጊዜ ቤቷ ስም አልነበራትም ብቻ "የጸሎት ቤት" እያሉ ይጠሯት ነበር። ስም መስጠትም ሐሳባቸው አልነበረም።

አንድ ቀን ምሽት፣ ከኤርትራ የመጣች አንዲት ኦርቶዶክስ እህት እዚያ ቤት መጣች። መንፈሳዊ ጭንቀት ላይ የነበረች ሲሆን፣ ወንድሞቹ ስለ እርሷ ጸለዩ  በጸሎቱ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ሥራውን ሠራ፣ እርሷም ከታሳዘባት ነገር ተፈታች።

ስትፈታ ስለ ቦታው መጠየቅ ጀመረች "ይህ ቤት ምንድን ነው? ስሙ ምን ይባላል?" "ምንም ስም የለውም፤ የጸሎት ቤት ነው" አሏት። እርሷም መልሳ "‘ቢታኒያ’ ለምን አትሉትም?" ስትል ጠየቀችው። ሐሳቡ ጥሩ መስሏቸው ተስማሙ፣ እና ከዚያን ቀን ጀምሮ "ቢታኒያ የጸሎት ቤት" ተባለች።

ኤርትራዊቷ እህት ዛሬም ኦርቶዶክስ ሆና ትኖራለች።

 

ከሌሎች ኅብረቶች ጋር መገናኘት

ቢታኒያ የጸሎት ቤት እያደገ ሲሄድ፣ መሪዎቹ በከተማው ውስጥ ከሚገኙ ሌሎች ተመሳሳይ የወጣት ኅብረቶች ጋር መገናኘት ጀመሩ። የቅዱስ ቄርቆስ ኅብረት፣ ከእስረኛ ሚካኤል አካባቢ የወጣው "የአዲስ አበባ አአማኑኤል" ኅብረት፣ የቀራኒዮ መድኃኔዓለም ቡድን፣ የአቡነ ረጋዊ ኅብረት (ራሳቸው)፣ የቅዱስ ገብርኤል ኅብረት፣ የለደታ ኅብረት ሁሉም በተናጥል እያደጉ ሳሉ እርስ በርሳቸው እንዲተዋወቁ ሆነ።

በዚህ ጊዜ የቢታኒያ ሰዎች ራሳቸውን እንደ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ይቆጥሩ ነበር። የጸሎት ኅብረታቸው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ሊተካ የመጣ አይደለም ለግል መንፈሳዊ ዕድገት ብቻ ነው።

 

ከቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ጋር የተፈጠረ ግጭት 

ግን ሁሉም ነገር ቀላል አልነበረም። በቤት ኅብረቶቹ ውስጥ የእግዚአብሔር መንፈስ በሚያስደንቅ ሁኔታ ይሠራ ነበር ሰዎች በመንፈስ ይሞላሉ፣ መናፍስት ይጨዋሉ፣ ወጣቶቹም በኢየሱስ ስም ገስጸው ያስወጡ ነበር።

ይህ ሁሉ ግን በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት የካህናት ብቻ ነው የነበረው። "ምእመን አጋንንት ማስወጣት አይችልም" የሚል ጥብቅ ስርአት ነበር። ስለዚህ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አጋንንት ሲጨዋ፣ ወጣቶቹ "በኢየሱስ ስም" ብለው ለማስወጣት አይደፍሩም ነበር  ይጋለጡ ይሆናል ብለው ይፈሩ ነበር። ምእመኑን በውስጥ ኮንታክት ለይተው ወደ ጸሎት ቤት ያመጡት ነበር፣ እዚያ ጸሎት ይደረግላቸው ነበር።

ሌላው ችግር ደግሞ የውጪ ስብከት ነበር። የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አውደ ምሕረት ላይ ሲሰብኩ፣ የኢየሱስ ስም በተደጋጋሚ ሲጠራ፣ "ይህ ሰው 'ኢየሱስ' አበዛ" የሚል ቅሬታ ይነሳ ነበር። ጴንጤ የመቅረብ ምልክት ተደርጎ ይቆጠር ነበር።

 

ኦርቶዶክስ ሆኖ ማገልገል 

ቢታኒያ ለረጅም ዓመታት የያዘችው ጥብቅ እምነት "ጌታን ለማገልገል ኦርቶዶክስ ሆኖ መቆየት ይቻላል" የሚል ነበር። "ጌታን ለማገልገል ግድ ጴንጤ መሆን አለበት" የሚለውን ሐሳብ ጨርሶ አይቀበሉም ነበር።

ለዚህም ነው ለረጅም ጊዜ ከየትኛውም ወንጌላዊ ድርጅት ጋር ራሳቸውን ሳያገናኙ፣ ራሳቸውን ችለው አገልግሎቱን ይቀጥሉ የነበሩት።

 

የመጀመሪያው ጉባኤና የአማኑኤል መውጣት

ቢታኒያ የመጀመሪያውን ትልቅ ጉባኤ  ዐሥራ አምስተኛውን ጉባኤ በዐሥራ አምስት ቀበሌ ለማድረግ ስታስብ፣ ምንም ዓይነት ሕጋዊ ዕውቅና አልነበራትም። አዳራሽ ለመከራየት ግን ዕውቅና ያስፈልጋል። ነገር ግን የናዝሬት አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን ቀደም ብሎ ይህን ሁኔታ ተረድቶ የራሱን ዕውቅና ከመንግስት አጊኝቶ ስለነበረ፣ ቢታኒያ በናዝሬት አማኑኤል ፍቃድ ሥር ጉባኤውን ማካሄድ ቻለች። ይህ የመጀመሪያው ኮንፈረንስ ነበር።

በወቅቱ የነበረው ትልቁ ጉድለት ግን ሸክም የተሰማው፣ ከመንግስት ጋር ያለን የዕውቅና ጉዳይን አስተባብሮ ሊያስኬድ የሚችል፣ ከጸሎት እና ከስብከት ባሻገር አሰላስሎ ዕቅድ የሚያወጣ፣ ስለህብረቱ ቀጣይ ዓላማና ርዕይ እንዲሁም  ቀጣይ አቅጣጫዎችን የሚያስቀምጥ መሪ ሰው አለመኖሩ ነበር። ስለዚህ ብዙ ነገር በሙሉ አቅሙ መጓዝ አልቻለም።

ከዚያ በኋላ የአዲስ አበባ አማኑኤል ራሱ ከኅብረቱ ወጣ ከወንጌላውያን ኅብረት ጋር በውስጥ ግንኙነት አድርጎ ይወጣ ጊዜ፣ ይከተሉ የነበሩ የቢታኒያ ሰዎች ሁኔታውን አይተው "እንዲህ ነው የሚገጥመን?" ብለው ወደ ኋላ ተመለሱ። የተሀድሶን ግስካሴ "ማኅበረ ግርሣኔ" የሚል ድምፅ ያስነሳ ቡድን "የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት ሊያፈርሱ ነው" የሚል ስጋት ሲፈጥር፣ አንዳንድ ሰዎች ሙሉ ለሙሉ ራሳቸውን አግልለዋል።

 

የመንፈሳዊ ማኅበር ምስረታ

ቀስ በቀስ ቢታኒያ የራሷን ተቋማዊ መሠረት መገንባት እንዳለባት ግልጽ ሆነ። በወቅቱ ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም። መደበኛ ዕውቅና ያስፈልግ ነበር።

ስለዚህ ወደ ፍትህ ሚኒስቴር ቀርበው ጥያቄ አቅርበው፣ "ቢታኒያ መንፈሳዊ ማኅበር" በሚል ሕጋዊ ዕውቅና አገኙ። ከዚያ ጀምሮ እንደ አንድ መደበኛ ማኅበር ሥራቸውን ቀጠሉ።

 

ከኦርቶዶክስ መንገድ መውጣት

ይህ የራቀ የለውጥ ሂደት "የአአማኑኤል ሁኔታ" በሚባለው ላይ ተወሰነ።

በውጭ ካለው ሰፊ የወንጌላውያን ልምድ ጋር በጥብቅ መገናኘታቸው  በተለይ ስለ መንፈስ ቅዱስ ሙላት፣ ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች፣ ስለ መንፈስ ቅዱስ ናፍቆት ያላቸው ልምድ ራሳቸውን አሁንም "ኦርቶዶክስ ነን" ብለው ለማቅረብ የማይችሉበት ደረጃ ላይ አደረሳቸው።

 

ኅብረቱ ለሁለት ተከፈለ

ኦርቶዶክስ ሆነው ለመቆየትና ከውስጥ ለማገልገል የመረጡት እኩል በቦታቸው ቀሩ። እነሱም በኋላ የራሳቸውን ቡድን አደራጅተው፣ ዛሬ "የአሁ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን" ተብሎ ይጠራል  በኦርቶዶክስ ዝማሬና አለባበስ ስታይል የሚያገለግል ለየት ያለ ቡድን ሆኖ ቀጥሏል። እንዲያውም በኋለኞቹ ጊዜያት እንደ ቤተ ክርስቲያን አድጎል። ቅዱስ ኪዳኔ "በረከቱ" እያሉ የሚያገለግሉ ቄሶች ስለ አሴቆል እንኳ የተማሩ አሉ።

ቢታኒያ ግን ሌላ መንገድ መረጠች  በወንጌላዊ መሠረት ላይ ራሷን አደራጀች።

 

ቤተ ክርስቲያን መሆን (1993 ዓ.ም.)

በ1993 ዓ.ም.፣ ድርጅቱ ስሙን ቀየረ  ከ"ቢታኒያ መንፈሳዊ ማኅበር" ወደ "ቢታኒያ ቤተ ክርስቲያን” ተቀየረ።

ይህ የስም ለውጥ ብቻ አልነበረም  ራዕይ ለውጥ ጭምር ነበር። ከዚያ ጀምሮ ቢታኒያ የራሷን አባልነት ማዘጋጀት፣ በጂኦግራፊ መስፋፋት፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት ማስፋፋት ላይ አሰላስላ መሥራት ጀመረች።

 

የዛሬዋ ቢታኒያ፡ መዋቅርና አገልግሎቶች

ቤተ ክርስቲያኗ አሁን በተደራጀ መልኩ ትሠራለች።

ከላይ የቦርድ አመራር አለ አምስት የቦርድ አባላት ያሉ ሲሆኑ፣ ቤተ ክርስቲያኗን በበላይነት ይመራሉ።

ከዚያ በታች የፓስተራል አመራር አለ። በአሁኑ ሰዓት ሁለት ሙሉ ጊዜ ፓስተሮች በመሪነት እያገለገሉ ነው፣ ሁለት ተጨማሪ በሥልጠና ላይ ናቸው። በአጠቃላይ አምስት ሙሉ ጊዜ አገልጋዮች አሉ።

 

የተለያዩ የአገልግሎት ክፍሎችም ተደራጅተዋል፦

• የትምህርት አገልግሎት (Education) ሥልጠናዎችን የሚያዘጋጅና ሌሎቹን የአገልግሎት ክፍሎች የሚደግፍ።

• የዝማሬ አገልግሎት (Worship/Music)

• የወንጌል ስርጭትና ተልኮ (Evangelism and Mission) ዋናው ተልኮ ይህ ነው።

• የለጉ ሳምራዊ አገልግሎት (Good Samaritan) በማኅበራዊ ድጋፍ ላይ የሚያተኩር። በአባላት ኮንትሪቡሽን ይደጋፋል፣ ለሌሎች ለመትረፍ የሚሠራ።

• የጸሎት አገልግሎት (Prayer) የጸሎት ስፍራዎችን የሚያመቻች።

• የቤት ለቤት ኅብረት (Home Cell Ministry) በየመኖሪያ አካባቢው ምእመናን እንዲገናኙ፣ የእግዚአብሔርን ቃል እንዲያጠኑ፣ እና በዙሪያቸው ላሉ ሰዎች ወንጌልን እንዲያደርሱ የሚደግፍ።

 

የሶስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ

ቤተ ክርስቲያኗ አሁን የሦስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ትሠራለች። ዓላማውም በወር ወር በዓመት የሚደረግ ጥቃቅን ዕቅድ ብቻ መሆን ሳይሆን፣ ሰፋ ያለ ራዕይ ይዞ ሁሉንም ነገር ማስተባበር ነው።

በዕቅዱ ውስጥ ዋናዎቹ ነጥቦች፦

• የአባልነት ቁጥር መጨመር

• በጂኦግራፊ መስፋፋት

• ወንጌል የመስበክን ሥራ ተቋማዊ ማድረግ በግል አገልጋዮች ላይ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን፣ መላው አካል የሚጋራው እንዲሆን

 

የሻሸመኔ አገልግሎት

ቤተ ክርስቲያኗ ሻሸመኔ አካባቢ የመሥራት ዕድል ያገኘችው በአንድ የቅርብ ሰው አማካይነት ነው። ይህ ሰው እዚያ የሚያውቀው ቡድን ነበረ በቋንቋ ችግር ምክንያት ከነበሩበት ቤተ ክርስቲያን ወጥተው ራሳቸውን ችለው የተደራጁ አምስት ቤተሰቦች።

እነዚህ ቤተሰቦች በኢኮኖሚ በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ስለነበሩ፣ ቢታኒያ የመንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን የቁሳዊ ድጋፍ መስጠት እንዳለበት ተረዳ። ቤት እንዲከራዩ አደረገች፣ መደበኛ የቤት ኅብረት ጀመረች፣ ከእነሱ ጋር ወንጌልን ሰበከች።

ነገር ግን አንድ ጥሩ ዓላማ ያለው ነገር መጥፎ ውጤት አስከተለ። የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ለመጀመር ብለው የልብስ ስፌት መሣሪያዎች ገዙ ግን አባላቱ እርስ በርሳቸው መግባባት ስላልቻሉ፣ የተጠበቀው እርዳታ ራሱ የመከፋፈል ምንጭ ሆነ።

ከዚያም በተለይ የቦታውን አገልግሎት ሲመራ የነበረው ሰው፣ ያንን ቦታ በራሱ ስም ቀይሮ መኖሪያ ቤት እንዲሆን አድርጎታል ተብሎ ተሰማ። እዚያ የነበሩ ሰዎች ደስ አልተሰኛቸውም ነበር፣ ስለዚህ ወደ ቢታኒያ ተመለሱ።

ዛሬ ቢታኒያ የቀረውን ቡድን ይዛ የቤት ኅብረቱን እያደራጀች ነው። እዛ ላሉት ሰዎች በትዕግሥት በተለያዩ ጊዜያት ፕሮግራሞችን እያደረገች እያደረገች ትገኛለች።

 

የ2014 ክፍፍል፡ "ማደረ መለኮት"

በ2014 ዓ.ም. አካባቢ፣ ቢታኒያ ሌላ የውስጥ ክፍፍል አጋጠማት።

በማንኛውም አጋጣሚ በቤተ ክርስቲያን/ ህብረት ውስጥ የግል ራዕይ ያለው ሰው፣ የሌሎችን ልብ ሳያገኝ የራሱን ሐሳብ ብቻ ለመፈጸም ሲሞክር፣ ግጭት መፈጠሩ የማይቀር ነው። የተወሰኑ ሰዎች በዚህ ምክንያት ከቢታኒያ ወጥተው፣ ዛሬ "ማደረ መለኮት ቤተ ክርስቲያን" በሚል ስም በአየርጤና  አካባቢ የራሳቸውን ጉባኤ መሥርተዋል።

ቢታኒያ የእርቅ ጥረቶችን አድርጋ ነበር። ስብሰባ፣ ንግግር፣ የእንባ ሰዓት  ሁሉም ተደርጓል። ግን ጉዳዩን በዋነኛነት የያዘው ሰው "በዚህ መልኩ መልሰን ሥራውን አንቀጥልም" አለ።

በወቅቱም "እንደ አጥቢያ (ቅርንጫፍ) ሆነን ብንቀጥል ይሻላልን?" የሚል ጥያቄ ቀርቦ ነበር። ግን አጥቢያ መሆን የሚቻለው ሰዎች በአንድ ጂኦግራፊያዊ አካባቢ ሆነው ሲሰባሰቡ ነው  የተለያየ ቦታ የሚኖሩ ሰዎች በግጭት ምክንያት የተሰባሰቡ አጥቢያ ሊሆን አይችልም። ስለዚህ ሐሳቡ አልተተገበረም።

ይህ ለቢታኒያ የቅርብ ጊዜ ቁስለት ነው። የልብ መከፋፈል አለ፣ ጉዳት አለ፣ ብዙ ሰዎች ከውስጡ ቆስለዋል።

 

ከፈተናዎች የተማርናቸው ትምህርቶች

በመጀመሪያ የቢታኒያ መሪዎች በሌሎች ቤተ ክርስቲያናት ላይ የሚሆኑ ችግሮች ይመለከቱ ነበር፣ "እንዴት እንደዚህ ይሆናል?" ብለውም ይጠይቁ ነበር። ቆይተው ግን ራሳቸው እንዳሉበት ተረዱ። እነዚያ ችግሮች ሁሉ በራሳቸውም ላይ ሊሆኑ ችለዋል።

ይህ ግን የተመቻቸ ቤተ ክርስቲያን ሕይወት ቢሆን ኖሮ ሊደርሱበት የማይችሉበትን ጥልቀት ሰጣቸው። ያጋጠሙት ችግሮች "እግዚአብሔር ማንነቱን እንዲገልጥላቸው" ምክንያት ሆኑ።

 

ስለ መጪው ጊዜ ራዕይ

የቢታኒያ ራዕይ የመነሻው 1ኛ ጴጥሮስ 2፡9 ላይ የሰፈረው ቃል ነው — "ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት ትናገሩ ዘንድ።"

ይህን ራዕይ በሁለት መንገድ ለማየት ይሞክራሉ፦

በመጀመሪያ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ውስጣዊ ሕይወት መታደስ በጸሎት የተሰማራ፣ የእግዚአብሔርን ቃል የሚያውቅና የሚማር፣ በተልኮ የተተከለ፣ የእርስ በርስ ፍቅርና አንድነት የሚተገብር ቤተ ክርስቲያን መሆን።

ሁለተኛ፣ በቁጥርም በጂኦግራፊም መስፋፋት። የተወሰኑ አገልጋዮች ብቻ ሳይሆኑ መላው አካል በወንጌል ሥራ ላይ የተሰማራ እንዲሆን ማድረግ።

ስልጤን በወንጌል መድረስ

በቤተ ክርስቲያኒቱ ጉባኤ በተካሄደ አንድ ወቅት፣ ወንጌል ካልተደረሰባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ዝርዝር ቀርቦ ነበር። ከእነዚህ መካከል የስልጤ አካባቢ "ወንጌል አልተደረሰበትም" ከሚባሉት መካከል ነበር።

ቢታኒያ የስልጤ አካባቢን እንደ ልዩ ዒላማ ይዛ  "ይህ አካባቢ ወንጌል እንዲደርስ" እያለች ራዕይ ላይ አስቀምጣዋለች። ሁሉንም ያልተደረሰ አካባቢ መድረስ ባይቻልም፣ ቢያንስ ስልጤን እንደ ዒላማ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመድረስ ጥረት ታደርጋለች።

የእግዚአብሔር ሥራ ምስክርነት፡ የጸሎት ቤቶቹ ታሪክ

የእግዚአብሔር አሠራር በቢታኒያ ጉዞ ውስጥ ግልጽ የሚታይበት አንዱ ቦታ የተለያዩ የጸሎት ቤቶች ይዞታ የነበራቸው አካባቢዎች ናቸው። እነዚህ ቦታዎች በሙሉ ጨለማ የነበረባቸው ኃይለኛ የመናፍስት አሠራር የሚካሄድባቸው ስፍራዎች ነበሩ።

ሀ) የመጀመሪያው ቦታ  "አምስተኛ"

የመጀመሪያው የጸሎት ቤት "አምስተኛ" በሚባለው አካባቢ ነበር  በከተማው ውስጥ በጣም ከከፋ የሆኑ አካባቢዎች መካከል አንዱ ነው። በወቅቱ ከአሜሪካ የመጡ የጤና ባለሙያዎች ስለ ኤች.አይ.ቪ./ኤድስ ትምህርት ሲሰጡ እንኳ የተመረጠ አካባቢ ነበር።  ቢታኒያ እዚያ ብዙ ጸለየች። ዛሬ ያ አካባቢ ተለውጧል ሕንፃዎች ተሠርተውበታል፣ ብዙ የቤተ ክርስቲያን አባላትም ከዚያ የወጡ ናቸው። ተስፋ መታየት ጀምሯል።

ለ) ሁለተኛ ቤት — ቀድሞ የጣኦት አምልኮ የሚደረግበት የነበረ ቤት

ከመጀመሪያው ወጥተው የገቡበት ሁለተኛው ቤት፣ ባለቤቱ ትልቅ ለጣኦት ዐምልኮ የሚሰግድ፣ የጥንቆላ ሰው ነበር  ። እዚያ እየጸለዩ፣ የጌታን ቃል እየሰሙ፣ እየዘመሩ ሳሉ፣ ከዚያ አካባቢ የነበረ አንድ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን መጥቶ ስለ ቤቱ ሁሉ መሰከረላቸው።

የቤቱ ባለቤት ልጆች አንዱ ከአንዱ እየታመሙ እየሞቱ ነበር  በተራ በተራ። መጨረሻ ላይ የመጨረሻው ልጅም በጠና ታመመ። እነዚህ ወንድሞች ለቤተሰቡ ጸለዩ፣ ጌታን እንዲቀበል ጥሪ አደረጉ  ቤተሰቡም አምኖ ተቀብሎ ዳነ።

ቤቱን ያከራየቻቸው እህት እራሷም ጌታን ተቀበለች። ሕይወቷ ተለውጦ፣ ከዚያ በኋላ በፀና እምነት እስከ ሞቷ ኖራለች።

 

ሦስተኛ ቤት “የአልማዝ ቤት”

ሦስተኛው ቤት የአልማዝ ነበር። እርሷ ራሷ ቀደም ብላ ጌታን የተቀበለች ጠንካራ እምነት ያላት ሴት ነበረች። ጋብቻዋም በጌታ ምክንያት ተፈትቶ ስለነበረ፣ የቢታኒያ ሰዎች ከእርሷ ጋር መኖር ለእርሷም ራሷ መጽናኛ ሆኖ ነበር።

 

 

ይቀጥላል!

Bethany
Bethany